የተጠናከረ የአፈር ግድግዳ (Reinforced earth)
Published 8. Juli 2024 22:32 by
አሰራር
ሰእል: የተጠናከረ የአፈር ግድግዳ
የተጠናከረ የአፈር ግድግዳ ተቆፍሮ ያለቀ ወይም በተፈጥሮ የሚገኝ ተዳፋትን ወይም የከፍታ ልዮነትን ከተዳፋቱ ፊት መከለያ ግድግዳ (የእንጨት፣ የድንጋይ ጋቢዮን ወይም የኮንክሪት ግድግዳ) በማቆም በግድግዳውና በተዳፋቱ መካከል አፈርን በመጠቅጠቅና በመሙላት እንዲሁም በተወሰነ የከፍታ ልዮነት ከግድግዳው ጋር የተያያዙ ረጅም፣ ጠፍጣፋና ቀጭን የሆኑ የብረት ገመዶችን ወይም አፈር ማጠናከሪያ ፕላስቲክ ንጣፎችን (geotextiles) በሚደለደለው አፈር ውስጥ በመቅበር የተደለደለው አፈር እርስ በእርሱ እንዲተሳሰር በማድረግ ግዙፍ የሆነ የመጠበቂያ ግድግዳ የመፍጠር ሂደት ነው።
የተጠናከረ የአፈር ግድግዳ ያለምንም የፊት መከላከያ ግድግዳ የተጋለጠውን ተዳፋት በጨርቅ ወይም በፕላስቲ በመሸፈንና እጽዋትን ከላዮ በማልበስም ሊከናወን ይችላል።
ሰእል: አፈር ማጠናከሪያ ፕላስቲክ ንጣፎችን (geotextiles)
ጥቅም
በብረት ገመዶች ወይም ፕላስቲክ ንጣፎች የተጠናከረ የአፈር ግድግዳ፣ ድልድዮችን ለመሸከም፣ በመንገድ እንዲሁም የባቡር መስመር ግንባታ ጊዜ ከመንገዱ ጎን የሚገኙ ተዳፋቶችን ለመጠበቅ፣ እንዲሁም ተዳፋቶችን በመሙላትና በመደልደል ለተለያየ አላማ ጥቅም ላይ የሚውሉ የተደለደሉ መሬቶችን ለመፍጠር ያገለግልላል።
በብረት ገመዶች ወይም ፕላስቲክ ንጣፎች የተጠናከረ ግድግዳ ከማጠናከሪያ ገመዶች እና ፕላስቲኮች ውጪ መሉ በሙሉ አፈርን በመጠቀም ስለሚሰራ ከኢኮኖሚና ከአካባቢ ብክለት አንጻር ከፍተኛ ትኩረት እየተሰጠው የሚገኝ የመሬት ደጋፊ የግድግዳ አይነት ነው።
ምጠና
የተጠናከረ የአፈር ግድግዳ የመሬት ግፊትን በአፈሩ የፍትጊያ ጥንካሬና በውስጡ በሚገኘው የማጠናከሪያ ብረት ገመድ ወይም የማጠናከሪያ ፕላስቲክ ንጣፍ የመለጠጥ ጥንካሬ አማካኝነት የሚቋቋም ሲሆን፣ አፈሩና የማጠናከሪያ ገመዱ ወይም ፕላስቲኩ የመሬት መንሸራተቱን ለመቋቋም የሚጀምሩት ወይም የሚነሳሱት የአፈር ሙሌቱ በሚያሳየው መጠነኛ የመንሸራት እንቅስቃሴ አማካኝነት ነው።
የተጠናከረ የአፈር ግድግዳ በግድግዳው ላይ ለሚያርፉ ውጫዊ ጫናዎችና (የመሬት ግፊት፣ ቁልል አፈር እንዲሁም የተሽከርካሪ ክብደት) በግድግዳው ውስጥ ለሚከሰቱ ውስጣዊ ጫናዎች መመጠን ይኖርበታል።
በውጫዊ ጫናዎች አማካኝነት ግድግዳው ሊገለበጥ፣ ሊንሸራተት ወይም በግድግዳው ክብደት አማካኝነት ከግድግዳው ስር የሚገኘው መሬት ሊሰረጉድ ወይም ሊፈርስ ሲችል፤ ሙሌቱና የማጠናከሪያ ጨርቁ በህብረት ውስጣዊ ጫናዎችን መቋቋም ሲያቅታቸው ደግሞ የግድግዳው አካል እርስ በእርሱ በመንሸራተት ሊፈርስ ወይም ሊሰበር ይችላል።
ጠቃሚ አድራሻዎች
አለም አቀፋዊ ወይም ሃገራዊ ደንቦች
-
EN 1997: Eurocode 7: Geotechnical design
-
EBGEO - Empfehlungen für den Entwurf und die Berechnung von Erdkörpern mit Bewehrungen aus Geokunststoffen (2010) DGGT (ጀርመንኛ)
ዋነኛ የማጠናከሪያ ፕላስቲክ ንጣፍ አምራቾች
ለምጠና የሚያገለግሉ ሶፍትዌሮች
Similar posts
0 comments
There are no comments.